የኩክየለሽ ማርያም ገዳም ከደ/ብርሐን በስተ ሰሜን ምስራቅ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኝ ሲሆን ገዳሟን የፈለፈሉት አባት አባ ኀይለ ጊዮርጊስ የተባሉ ጻድቅ አባት ሲሆኑ እኚህ አባት በቡልጋ አውራጃ ከእናታቸው ከወ/ሮ በለጤ ከአባታቸው ከአቶ ዳርጌ በ1908 ዓም ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በ64 አመታቸዉ በእግዚአብሄር አጋዥነት በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት 4(አራት) ቤተ መቅደሶችና ሌሎች የባህታዊያን መኖሪያ ፈለፈሉ ከተፈለፈሉት ቤተ መቅደሶች ድንቅ ታምር ያላት የኩክየለሽ ማርያም ፍልፍል ቤተመቅደስ በገዳሙ ግርጌ የሚገኝ ነዉ፡፡ኩክየለሽ ማርያም ማለት የስሟ ትርጓሜ የጀሮ ኩክ የሌላት የነገሯትን ፈጥና የምትሰማ የምህረት እናት ማለት ሲሆን በዚሁ ገዳም እስከ 2000 ዓም ድረስ በእምነተ ብቻ ምእመናንን ስትባርክ ድዌያንን ስትፈውስ ቆይታለች እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ መስከረም 21/2001 ዓም ጠበሏ ፈልቆ እና ተባርኮ ለምእመናን ድኅነትን እየሰጠችና እየባረከች ትኖራለች በዚህ ጠበል በህመም በመንፈስ ችግር የሚሰቃዩ ምእመናንን ወደ ገዳሙ እየመጡ ደህነትን እያገኙ ይመለሳሉ፡፡ ይህ ቦታ ለተቸገሩ ለተጨነቁ መፍትሄ ላጡ መፍትሄ የሚያገኙበት የመማጸኛ ቦታ ሆኗል፡፡የገዳሙ ቃል ኪዳን መጥቶ ደጁን የረገጠ 7 ትዉልድ ምህረት ይደረግለታል፡፡በበለጠ የገዳሙን ታሪክ ከቦታዉ ሄደው ይማሩ፡፡
አባ ኃይለጊዮርጊስ የኩክ የለሽ ማርያም ገዳምን የመሰረቱ ታላቅ አባት በመስከረም 23 ቀን 1903 ዓ.ም በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ተወለዱ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ በእርጅና ጊዜአቸው በ64 ዓመታቸው ለመንፈሳዊ አገልግሎት ወደ ቤቱ የጠራቸው በአካለ ሥጋ በነበሩበት ጊዜም ነበር፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱሳን መላእክት ከጻድቃን ሰማዕታት ጋር ለመነጋገር የበቁ የወንጌሉን ቃል በሕይወት በመኖር የሚሰብኩ ታላቅ አባት ነበሩት አባ ኃ/ጊዮርጊስ እግዚአብሔር ያከበረውን ማን ያዋርደዋል እንዳለ መጽሐፉ እኚህ ታላቅ አባት በሣርያ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሲገለገሉ አና ሲያገለግሉ ቤተክርስቲያን ሲረዱ የቀዩ ቆይተው ከዕለታት አንድ ቀን በሰኔ ወር 11ለ 12 ለሊት በዋዜማው ከቅዱስ ሚካኤል ጋር በመነጋገር የሥላሴን ዙፋን ገነትንና ሲኦልን ለማየት የበቁ አባት ናቸው፡፡
አባ ኃይለ ጊዮርጊስ በእግዚአብሔር አጋዥነት በቅዱሳን መሪነት ገዳሙን የመሰረቱት ሲሆን ከድንጋይ ፍልፍል አራት / 4 / ቤተ መቅደሶችንና ሌሎች የባህታውያን መኖሪያ ዋሻዎች የሰሩ ሲሆን አብረዋቸው ቅዱሳን መላእክት እንደሚያግዟቸው በህይወት በነበሩበት ሰዓት ይናገሩ እንደነበር የገዳሙ አገልጋዮች ይናገራሉ።
እኚህ አባት ገዳሙን መስርተው ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት ካገለገሉ በኃላ በ1997 ዓ.ም መጋቢት 19 ቀን በዓለ እረፍታቸውን ካደረጉ በኃላ አጽማቸው በገዳሙ በጸሎት በአታቸው ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህ ገዳም ከ25 በላይ መለኮሳት የሚኖሩበት ተዓምራዊ ምድር ነው።ይህን ታላቅ ገዳም የረገጠ ወንድ የ40 ቀን ህጻን ሴት የ80 ቀን ህጻን ይሆናል ተብሎ ቃል ኪዳ ተገብቶለታል። እንዲሁም በቦታው የበረከት ሥራ የሰራ ጸሎት ያደረገ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ ምህረት እንደሚደረግለት ቃል ኪዳን ተገብቶለታል።
በአሁኑ ሰዓት ገዳሟ በሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ምክንያቶች አደጋ የተደቀነባት ሲሆን በአለም ያለው ምዕመን በረከት እንዲያደርግ ጥሪ ተደርጎለታል።
የቅዱስ እግዚአብሔር አብ ፍልፍል ዋሻ፡- ይህ ገዳም አባ ኃይለ ጊዮርጊስ በ1972 ዓ.ም ጀምረው በ1976 ዓ.ም ያጠናቀቁት ሲሆን ይህን ያህል ጊዜ ለምን እንደፈጀ የራሱ የሆነ ምክንያት አለውና በቦታው ተገኝተው ሚስጢሩን እንዲያውቁ ይመከራሉ።
ኩክ የለሽ ማርያም ፍልፍል ዋሻ፡- በ1984 ዓ.ም ጀምረው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው ያጠናቀቁት፡፡
የቅድስት ሥላሴ ፍልፍል ዋሻ፡- በ1984 ዓ.ም ጀምረው ከኩክ የለሽ ማርያም ፍልፍል ዋሻ ጋር አብሮ በአንድ ዓመት ውስጥ ነው የተጠናቀቀ ሲሆን በዚህ ዋሻም ድንቅ ተዓምራት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ምን ያምር ቅዱስ ገብርኤል፡- በ1986 ዓ.ም ጀምረው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ያጠናቀቁት ዋሻ ነው፡፡
ይህ ገዳም በቅዱስ ገብርኤል መሪነትና አጋዥነት በአባ ኃይለ ጊዮርጊስ ተፈለፈለ፡፡ በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ ጸበል ፈልቆ ብዙ ተዓምራትን እያደረገ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ በአራቱም ቤተመቅደስ በየእለቱ ማይጠንት ይታጠናል፡፡ እንዲሁም በየወሩ ቅዳሴ ይቀደስባቸዋል፡፡ገዳሙ በ1972 ዓ.ም ተጀምሮ በ1986 ዓ.ም መጨረሻ ተጠናቆ በ1987 ዓ.ም በአባቶች ተባርኮ መለኮሳት በምነና ሕይወት ገብተዋል፡፡